ኮሮናቫይረስ

የኮቪድ19 ስርጭትን ለመከላከል የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

By Abrham Fekede

March 29, 2021

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሰዎች እንቅስቃሴና ማህበራዊ ተግባራት ላይ ክልከላ የሚጥልና በወንጀል የሚያስጠይቅ መመሪያ ይፋ አድርገዋል።

መመሪያውን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይም እስከ 3 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች እንደሚያስቀጣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።

በመመሪያው መሰረት ማንኛውም የኮሮና ቫይረስ ያለበት ግለሰብ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ ተከልክሏል::

ቫይረሱ የተገኘበት ሰውም ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፣ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚያስችል ሁኔታም ንክኪ ማድረግ በህግ የሚያስቀጣ ሆኗል::

በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርግ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ÷ የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ያላደረገ ሰውን እንዳያስተናግዱ መመሪያው ያዛል::

የትራንስፖርት የስፖርትና ሌሎች ማህበራዊ መሰባሰቦችን በሚመለከትም ተቋማቱ በሚያወጧቸው ዝርዝር ደንቦች የሚፈፀሙ ይሆናል ተብሏል::

ስብሰባን በሚመለከትም ማንኛውም ሰብሳቢ አካል ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባራትን በመከወን የተሰብሳቢዎችን ቁጥር 50 ብቻ እንዲሆን ተወስኗል::

አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ለሰላም ሚኒስቴርና ለጤና ሚኒስቴር እንዲያሳውቅ መመሪያው አስቀምጧል::