አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለብልጽግና ሴቶች ሊግ በመደመር እሳቤ እና በብልጽግና ፓርቲ ሕገ ደንብ ዙሪያ በሃዋሳ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ሊቀ መንበር ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ፥ አንድ የፖሊተካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት፣ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ለማጠናከር እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ለማጠናከር በማሰብ ውህደት መደረጉን ተናግረዋል።
አጋር የሚለውን አግላይ የፖለቲካ አካሄድን በመናድም በመደመር እሳቤ ለሁሉም ሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስርዓት እየተገነባ ነውም ብለዋል።
አያይዘውም የፓርቲው እሴት ሃገር የመገንባት ሂደት መሆኑን ጠቅሰው፥ ሴቶች ሃገር ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የሚያውኩ ተግባራትን በመከላከል ለሰላም ዘብ በመቆም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ከዚህ ባለፈም በፓርቲው ህገ ደንብ መሠረት ሁሉንም ሴቶች ባካተተ መልኩ የአደረጃጀት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ሴቶች ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሀላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
በስልጠናው ፓርቲው ባዘጋጀው ሕገ ደንብ ዙሪያ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፥ በመደመር እሳቤ ላይም ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችል ስልጠና ይሰጣል ተብሏል፡፡ በስልጠናው ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ ሴት አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።