Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖሊዮ ክትባት ከነገ ጀምሮ እስከ መጋቢት 20 እንደሚሰጥ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እስከ መጋቢት 20 እንደሚካሄድ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ ዘመቻውን አስመልክተው እንደገለጹት፣ የክትባት ዘመቻው ከመተከል ዞን ውጪ በሚገኙ የክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ይካሄዳል፡፡

ቤት ለቤት በሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት 124 ሺህ 497 ህጻናት እንደሚከተቡ ይጠበቃል፡፡

ክትባቱ ቤት ለቤት የሚሰጥ በመሆኑ በመተከል ዞን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በዞኑ ዘመቻውን ማካሄድ እንዳልተቻለ የተናገሩት አቶ ፈቃዱ፣ በቀጣይ ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ሲፈጠር ዘመቻው ይካሄዳል ብለዋል፡፡

የቅድመ-ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የጠቆሙት ኃላፊው ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ክትባቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ቀድመው መድረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለክትባት ዘመቻው መሳካት አመራሩ፣ ወላጆች፣ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ማቆያ ትምህርት ቤቶችና መላው ህብረተሰብ የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ፈቃዱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፍት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version