አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርጫውን ለመታዘብ 155 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው 36 ድርጅቶች በ1ኛ ዙር ፍቃድ ማግኘታቸው ተገልጿል።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመዘገባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዘርፉ በሚሰማሩበት ወቅት በዓላማቸው መሰረት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ተብሏል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫው የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ኤጀንሲ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማግባባት፣ የመራጮች ትምህርት እና ምርጫ መታዘብ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።
የውጭ ድርጅቶች በምርጫ መታዘብም ሆነ ማስተማር በልዩ ሁኔታ በምርጫ ቦርድ ካልተጋበዙ በቀር ምንም ሚና አይኖራቸውም ሲሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ተናግረዋል።
አጀንሲው በቁጥጥር ስርዓቱ ማህበራቱን በህግ መሰረት መስራታቸውን መከታተል፤በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት መስራታቸውን እና ጥቆማን መሰረት በማድረግ ምርመራ እንደሚያካሄድም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ማህበራት ህግ ጥሰው ሲገኙ የማስጠንቀቅ፣ ዕግድ የማድረግና የመሰረዝ ተገቢ እና ህጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማግባባት፣ግፊት ማድረግ፣ተጽዕኖ ማድረግ/የሙግት ስራ/ፖለቲካ አድቮከሲ ስራ/፣ መራጮች ትምህርት እና ምርጫ መታዘብ ላይ እንዲሳተፉ እና እንዲሰሩ አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 እንደሚደነግግ ያብራራል፡፡
ከዚህ አንጻር ድርጅቶቹ ከምርጫ በፊት የመራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ጊዜ ምርጫን መታዘብና ከምርጫ በኋላ ግጭት እንዳይከሰት ህዝቦችን የማረጋጋት እና አለመግባባቶች ቢኖሩ እንኳን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የማድረግ ሚና እንዳላቸው ተነግሯል፡፡
በመለሰ ምትኩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን