የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን በሶስት ዓመታት ውስጥ መካከለኛ የብድር ጫና ወዳለባቸው ሀገራት ለማሰለፍ እየተሰራ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ

By Abrham Fekede

March 23, 2021

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ የብድር ጫና ወዳለባቸው ሀገራት ለማሰለፍ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡

በ2010 ከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ካለባቸው ተርታ እንደነበረች የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሜርሻል ብድር ሙሉ በሙሉ ማቆም አለባት የሚል አቋም ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተሰራው ስራም በ2010 ዓ.ም 36 ነጥብ 6 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ጫና በ2011 ዓ.ም ወደ 29 በመቶ እና በ2012 ዓ.ም ወደ 26  ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የብድር ጫናው በሦስት ዓመታት ውስጥ የ10 በመቶ እንደቀነሰ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት በተመለከተም ላለፉት 15 ዓመታት እየተደማመረ የመጣ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማይክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ ዋነኛው ችግርና ለውጥ ማምጣት ያልቻልንበት የዋጋ ግሽበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ግሽበቱ የሚጎዳው ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለውን ሕብረተሰብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማካይ የምግብ ወጪ 54 በመቶ፣  የቤት ኪራይ 16 እስከ 20 በመቶ፣ አልባሳት 5 እስከ 6 በመቶ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሕብረተሰብ ክፍሎች ወጪ እንደሆኑ አስታውሰዋል።

የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ቢሰራባቸው 80 በመቶ ጫና እናቀላለን ብለን እናምናለን፣ ያንን የተመለከተ ሥራ እያከናወንን ነው።

የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ስግብግብ ነጋዴዎች፣ ላትርፍ የሚለው አካል እና ዓለም አቀፍ ሁኔታው ሌሎች ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ ራሱን የቻለ ቡድን ይህን ችግር ለመቅረፍ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከገንዘብ ፖሊስ አንጻር ቁጠባ 25 በመቶ ማደጉን፣ የብድር አቅርቦት 38 በመቶ ማደጉንም አንስተዋል፡፡

የብር ኖት ለውጡን ቁጠባው እንዲያድግ፣ ገቢ እንዲጨምር 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የባንክ ደብተር እንዲያውጡ ማስቻሉንም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 90 ቢሊየን ብር ቁጠባ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

ባንኮች በ2010፤ 730 ቢሊየን፣ በ2011፤ 899 ቢሊየን ብር፣ በ2012፤1 ነጥብ 4 ትሪሊየን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ በስድስት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ትሪሊየን መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ባንኮች በ2010 170 ቢሊየን ብር ሲያበድር ለመንግስት 55 በመቶ ለግል ዘርፉ 45 በመቶ አበድረዋል፡፡

ይህ ቁጥር በ2013 ዕድገት አሳይቶ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ ከሰበሰቡት 155 ቢሊየን ብር ውስጥ 74 በመቶ ለግል ዘርፉ ቀሪውን ለመንግስት ማበደሩን አንስተዋል፡፡

ባንኮች ለግል ዘርፉ የሚያበድሩት ብድር ባለፉት ዓመታት እየጨመረ እንደመጣ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2011፤ 61 በመቶ እንዲሁም በ2012፤ 70 በመቶ አድጓል፡፡

ይህም የስራ አጥ ቁጥሩን ከመቀነስ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያመጣ ነው የጠቀሱት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሲሚንቶን በመሰሉ ምርቶች ላይ የሚታየው እጥረትም የዚህ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለው የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ትንሽ ከተሰራበት ብዙ ቱሪስቶች በመሳብ የገቢ ምንጭን ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላት  የቱሪዝም ሀብት ላይ መስራትና ማወቅ የገቢ ምንጫችንን ከማሳደጉም በላይ እርስ በርስ ለመተዋወቅም ይጠቅመናል ነው ያሉት።

ከተባበርን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተዓምር መስራት እንችላለንም ብለዋል።

በአይሲቲ በኩልም እድገት አምጥተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስሩ÷ በዚህ ሁለት አመት ውስጥ ስፔስ ላይ ስማቸው ከሚጠሩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለችም ነው ያሉት።

ዓለም ላይ ያላቸውን ደመናን ወደዝናብ የቀየሩ አገራት ጥቂት አገራት ናቸው ብለዋል፡፡

እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼ አየዋለሁ ብዬ ከምቀናባቸው ነገሮች አንዱ ይሄ የተከማቸ ደመና በተመረጠ ሁኔታ ማዝናብ መቻልን ነው ብለዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ይሄንን አቅም ገንብታ  ባለፉት ሳምንታት በሰሜን ሸዋ እና በጎጃም ያያችሁት ዝናብ የተፈጥሮ ሳይሆን እኛ ያዘነብነው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን