Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሙስናን ለመከላከልና ጠንካራ የስራ ባሕል ለማዳበር ብርቱ ጥረት አድርገዋል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ሙስናን በመከላከል ጠንካራ የስራ ባህል እንዲዳብር ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን አዲስ አበባ በሚገኘው የታንዛኒያ ኤምባሲ በመገኘት ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ ለታንዛኒያ ሕዝብና መንግስትና ለፕሬዚዳንቱ ቤተሰቦች በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንዲሁም በራሳቸው ስም ባስተላለፉት መልዕክት ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ለሃገራቸው ታንዛኒያ እድገትና ሠላም ለማምጣት ባደረጉት ጥረት ሲታወሱ እንደሚኖሩ ነው የገለጹት።

ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል እንዲሁም በዜጎች መካከል ጠንካራ የስራ ባሕል እንዲፈጠር ስላደረጉት ጥረትም እንዲሁ።

ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መልካም ወዳጅ ነበሩ ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፤ ከስድስት ሳምንታት በፊት ዳሬሰላም ላይ ሲያገኟቸው ሙሉ ጤነኛ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በወቅቱ የሁለቱን ሃገራት ትብብር ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ውጤታማ ውይይት አድርገን ነበርም ብለዋል።

ጆን ማጉፉሊ ለሃገራቸውና ለአፍሪካ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ታላቅ መሪ በመሆናቸው ሁላችንም አጥተናቸዋል በዚህም ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።

በኤምባሲው ቅጥር በመገኘት ባሰፈሩት የሐዘን መግለጫ የፕሬዚዳንት ማጉፉሊን መልካም ስብዕና፣ ለሃገራቸው፣ ለአፍሪካም ሆነ ለሰው ልጆች የነበራቸው ክብር ሁልጊዜም ሲያስታውሱ እንደሚኖሩ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ባጋጠማቸው የልብ ሕመም ሳቢያ በዳሬሰላም ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ61 ዓመታቸው ባለፈው ሣምንት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ጆን ማጉፉሊ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት በ56 ዓመታቸው በፈረንጆቹ  2015 ነበር።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version