Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ በረከት ስምዖንን የመከላከያ ምስክሮች ቃል ማድመጥ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእነ አቶ በረከት ስምዖንን የመከላከያ ምስክሮች ቃል ማድመጥ ጀምሯል።

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 30 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ዓቃቤ ህግ አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለተመሰረተባቸው ክስ ያቀረቧቸውን የመከላከያ ቃል ምስክሮች ለማዳመጥና የሰነድ ማስረጃዎች ለመመልከት ለጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወቃል።

በወቅቱ ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎትም የተከሳሽ ጠበቆች በ4ቱ ክሶች አሉን ያሏቸውን የሰነድና 11 የቃል መከላከያ ምስክሮች አቅርበዋል።

ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በተሰየመው ችሎት ደግሞ የተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች የምስክር ቃል ከማሠማታቸው በፊት ተከሣሳሾች የተከሰሱበትን ቃል በማቅረባቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ቃል ለማዳመጥ በድጋሜ ለጥር 5 ቀን 2012ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤትም በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎትም የተከሳሽ ጠበቆች አሉን ካሏቸው 11 የቃል ምስክሮች አራቱን ያቀረቡ ሲሆን፥ ሶስቱ ግን ሊቀርቡላቸው እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች ካቀረቧቸው አራት የቃል ምስክሮች ውስጥ የአንደኛውን ቃል አድምጧል።

የቃል ምስክሩ በደቨንቱስ ስማርት ሜትር የውሃና የመብራት ብክነት አቅረቦት መቆጣጠሪያ ስራ መጀምር አስመልክቶ የምስክርነት ቃሉን አሰምቷል።

የምስክርነት ቃሉን ያሰማው የመከላከያ ምስክር ፕሮጀክቱ ወደ ማምረት ስራ መግባቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ዓቃቤ ህግ በበኩሉ ጀመረ የተባለው የደቨንቱስ የስማርት ሜትር በውሃና ኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ የጥረት ቦርድ ያልወሰነበት እና የጥራት ማረጋገጫ የለውም በማለት ተከራክሯል።

ለቀረቡት የመከላከያ ምስክሮችም ግልጽነት ይጎድላቸዋል ለተባሉ ጉዳዮች ከሳሽ አቃቤ ህግ መስቀለኛ ጥያቄ አቅርቦ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል።

ችሎቱ የቀረቡትን ምስክሮች ካዳመጠ በኋላም ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለማድመጥ ለነገ ማለትም ለጥር 6/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።

በናትናኤል ጥጋቡ

Exit mobile version