Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለሀገራዊ ምርጫው ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃኖችን በእኩልነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ የአሰራር ደምብ መዘጋጀት እንዳለበት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለሚካደው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች መገናኛ ብዙሃኖችን በእኩልነት እንዲጠቀሙባቸዉ ለማድረግ የአሰራር ደምብ መዘጋጀት እንዳለበት ተገለፀ፡፡

ሀገራዊ ምርጫው በተሻለ እና ዴሞክራሲያዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን መገናኛ ብዙሃኖች የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ፌደራላዊ ጎንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ መገናኛ ብዙሃኑ ፓርቲዎቸን ወይም ግለሰቦችን ሳይሆን ሂደቱን ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ ሚዛናዊ መረጃዎችን ለተከታዮቻቸዉ ማድረስ አለባቸዉ ብለዋል።

ባለፉት የምርጫ ጊዜያት መገናኛ ብዙሃኖቹ በአብዛኛዉ የመንግስት ልሳን የመሆን አዝማሚያ ታይቶባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ  ይህ አካሄድ በመጪው ምርጫ ሊስተካከል እና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለተከታዮቻቸዉ ማድረስ እንዳለባቸዉ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አረጋዊ በርሄ  በበኩላቸው እስከአሁን ባለዉ እንቅስቃሴ የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች አስፈላጊዉን ሽፋን ሰጥተዉናል ብለዋል፡፡

በቀጣይነት ሁሉም ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች  በእኩልነት የሚጠቀምባቸዉ ሚዲያዎች እንዲኖሩ የአሰራር ደምብ መዘጋጀት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

Exit mobile version