አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) በኮሮና ቫይረስ ታመው ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ የመተንፈሻ መሳሪዎች እጥረት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የኮሮና ህክምና ማዕከላት ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
ከመሳሪያዎች እጥረት ባለፈም ላሉት የመተንፈሻ መሳሪያዎች የመለዋወጫ እቃዎች ባለመኖራቸው ችግሩን ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ19 ህክምና ማዕከል የፅኑ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ህሩይ አርዓያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ የቫይረሱ ታማሚዎች ቁጥር ከቀን ቀን እያሻቀበ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ካሉት 22 የፅኑ ህክምና አልጋዎች ውስጥ ሁሉም መያዛቸውን የሚገልጹት ዶክተር ህሩይ ከእነዚህ ውስጥም 65 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
የሚሊኒየም ኮቪድ19 ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ በበኩላቸው፥ የማህበረሰቡን መዘናጋት ተከትሎ አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ፡፡
በዚህ ሳቢያም ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሁሉንም ጽኑ ህሙማን ማስተናገድ አለመቻሉን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም የመተንፈሻ መሳሪዎችን እገዛ የሚፈልጉ ህሙማን መበራከታቸው ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ያሉት የመተንፈሻ መሳሪያዎች ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ አገልግሎት የሰጡ በመሆናቸው አሁን ላይ ያላቸው አቅም ዝቅተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የኮሮና ታካሚዎች መብዛት የህክምና ማዕከላትን ከማጨናነቁ ባለፈ በባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም ዜጎች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች በትክክል ገቢራዊ እንዲያደርጉ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!