አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ምዕመናን የሰላም ምሳሌ በመሆን የሃገሪቱን ሰላም እንዲያስጠብቁ የሃይማኖት መሪወች ጥሪ አቀረቡ።
“ሀይማኖቶች ለሰላም በሚል ርዕስ” በሰላም ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተዘጋጀ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ ከዚህ ቀደም የነበሩ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች መልካቸውን ቀይረው ወደ እምነት ተቋማት እየገቡ ስለመሆኑ ተነስቷል።
ይህም ለዘመናት በሃይማኖት መከባበር እና በባህላዊ እሴቱ ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ ለማለያየት እና ወደ ግጭት ለመምራት ታቅዶ በጥቂት ሰዎች እየተሰራበት ነው ተብሏል።
ድርጊቱ ምንም እንኳን በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ግራ መጋባት መፍጠር ቢጀምርም፥ ለዘመናት በቆየው አብሮነት የጠነከረው የህዝቡ አንድነት የታሰበው ጥፋት እውን እንዳይሆን አድርጎታልም ነው የተባለው።
የሃይማኖት መሪዎችም ምዕመናን የሰላም ምሳሌ በመሆን የሃገሪቱን ሰላም እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከእናትና አባቶች የቆየውን መልካም ልምድ ለልጆች በማውረስ ሃገር የመጠበቅ ግዴታን መወጣት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ በእምነት ስም እየተፈጠሩ ያሉ ልዩነቶች እና ግጭቶች የእምነት አባቶች እና ተቋማት ራሳቸውን መልሰው እንዲያዩና እንዲፈትሹ የሚያደርጉ መሆን እንደሚገባቸው ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም አብሮነቱ የፈጠረው አንድነት እስካሁን ለከፉ ጉዳት ባይዳርግም ሁኔታዎች ግን መለስ ብለን ራሳችንን እንድናይ የሚያስገድድ ደረጃዎች ላይ መድረሳቸውን የሚጠቁሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቃለሂወት ቤተክርስቲያን ምክትል ዋና ፀሀፊ ዶክተር ኤርሚያስ ማሞ በበኩላቸው ወጣቶች በቤተ እምነቶቻቸው የሚያገኙትን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አንስተዋል።
የእምነት አባቶችም በንግግር ብቻ ሳይሆን በድርጊት ለተከታዮቻቸው አርአያ ሆነው መታየት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።
ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተያየታቸውን ለጣቢያችን የሰጡት አባ አበራ ገብረማርያም ከእምነት አስተምህሮ ባሻገር ባህላዊ የማህበረሰቡ እሴቶች እዚህ ላይ ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።
ከቤት እና ከአካባቢ የሚጀምሩት የስነ ምግባር መርሆዎችም ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ሰፊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ በወላጆችም ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባልም ነው ያሉት።
በመድረኩ ሁሉም የእምነት ተቋማት ለሀገር ሰላም መቀጠል ወሳኝ በሆነው መልካም ዜጋን በመፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።
በትእግስት አብርሃም