የሀገር ውስጥ ዜና

ለህዝብ የቀረቡ ፖሊሲና ስትራቴጅዎች ማዘጋጀታቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

By Tibebu Kebede

March 10, 2021

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህዝብ የቀረቡ ፖሊሲና ስትራቴጅዎችን ማዘጋጀታቸውን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብት ፍትሃዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ ፖሊሲና ስትራቴጅ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፣ ፓርቲያቸው በቅጥር ላይ ትኩረት ካደረገ የስራ እድል ፈጠራ ይልቅ ፈጠራን ለሚያበረታ አዳዲስ እይታዎች ትኩረት መስጠቱን ይናገራሉ፡፡

የኢንቨስትመንት ፣ የመሬት እና አርሶ አደሩን የተመለከቱ ጉዳዮችም በፓርቲው ፖሊሲና ስትራቴጅ ላይ ተመላክቷልም ብለዋል ሊቀመንበሩ ፡፡

የአብን ፖሊሲና ስትራቴጅ ክፍል ሃላፊ አቶ አዲስ ሃረገወይን በበኩላቸው፥ ውጤታማ መሆን የተሳነውን የግብርና መር ኢኮኖሚ ለማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ውጤታማ ለማድረግ ፓርቲያቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የስራ እድል ፈጠራን የሚያበረታቱ ፣ የጤና እና ሌሎች መስኮችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲና ስትራቴጅ ቀረጻ ስለመከናወኑም ይናገራሉ፡፡

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዘኑር አብዱልወሃብ ም ፓርቲያቸው በዋናነት የትምህርት ስርአቱን ለማሻሻል ትኩረት መስጠቱን አውስተዋል ፡፡

የትምህርት ስርአቱ ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በዘርፉ ከፍ ልምድ ያላቸውን ሙያተኞች በማሳተፍ የፖሊሲና ስትራቴጅ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል ፡፡

ከዚህ ባለፈም ሌሎች መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ የፖሊሲና ስትራቴጅ ቀረጻ ስለመከናወኑም አብራርተዋል ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተጠባቂው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ እና የዴሞክራሲ ማሳያ ይሆን ዘንድ ከሁሉም ሃላፊነት ይጠበቃልም ብለዋል ፡፡

በአወል አበራ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!