ጤና

ከልብ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር የኩላሊት በሽታ ተጋላጭነትን እንደሚያሳድግ ጥናት አመላከተ

By Tibebu Kebede

January 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍቢሲ) ከልብ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ለኩላሊት በሽታ የመጋለጥ እድልን እንደሚያሳድገው አንድ ጥናት አመላከተ።

በአሜሪካ የተደረገው ይህ ጥናት 9 ሺህ 47 ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን፥ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም ከልብ ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮችና በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ችግር ተጋላጭ ያልሆኑ ናቸው።

ከ17 አመታት በላይ በወሰደውና ከሰሞኑ ይፋ በሆነው ጥናት መሰረት ታዲያ ከልብ ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮች የተዳረጉ ሰዎች ለኩላሊት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው በ10 እጥፍ ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል 2 ሺህ 598 ሰዎች ከልብ ህመም ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮች ተጋልጠዋል።

ከዚህ ውስጥ ለልብ የደም ቧንቧ ችግር የተጋለጡ 210 ሰዎች ለኩላሊት በሽታ ተዳርገዋል ነው የተባለው በጥናቱ።

ተመራማሪዎቹም በልብ የደም ቧንቧ ችግር የተጋለጡ ሰዎች ለኩላሊት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን የጥናታቸውን ውጤት ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ ልብ እና ኩላሊት ካላቸው ተደጋጋፊ የስራ ባህሪ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።

ምንጭ፦ www.upi.com