የሀገር ውስጥ ዜና

የሱዳን ህዝብ ኤልሲሲን የተቃወማቸው ግብጽ ፍላጎቷን በሱዳን በኩል ለማስፈጸም እያሴረች መሆኑን በመገንዘብ ነው – ሱዳናዊ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ

By Abrham Fekede

March 10, 2021

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን ህዝብ ፕሬዚዳንት ኤልሲሲን የተቃወማቸው ግብፅ ፍላጎቷን በሱዳን በኩል ለማስፈጸም እየሠራች ያለውን ሴራ በመንቀፍ እንደሆነ አቶ ሀሊ ያሂያ የሚዲያ ባለሙያና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ።

አቶ ሀሊ ያሂያ ከሰሞኑ ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ካርቱም በተገኙበት ወቅት የህዝብ ተቃውሞ የገጠማቸው ግብፅ ፍላጎቷን በሱዳን ላይ ጭና ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገውን ሴራ በመቃወም ነው።

ግብፅ በሰሜን ምሥራቅ በኩል የሱዳንን ሰፊ መሬት በጉልበት ወራ መያዟ ህዝቡን እያስቆጨው ያለ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ሀሊ፣ ግብፅ አሁን የሱዳን ተቆርቋሪ መስላ መቅረቧ ለሱዳን አስባ አለመሆኑን ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።

የሱዳን ህዝብ የህዳሴው ግድብ መገንባት ጥቅም እንደሚሰጣቸው ያውቃሉም ብለዋል አቶ ሀሊ፡፡

በተጨማሪም ግብፅ የአስዋንን ግድብ በገነባችበት ጊዜ 27 ሰፈራ መንደሮች እና ከ3 ሚሊየን በላይ የቴምር ዛፎች ተጥለቅልቀዋል፤ 500 መቶ ሺህ ሱዳናዊያን ተፈናቅለዋል፤ ለዚህ ሁሉ ጥፋታቸው ምንም ዓይነት ካሳ ሳይሰጡ ይባስ ብለው መሬታቸውን በመውረራቸው የሱዳን ህዝብ እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚቃወማቸውም አመልክተዋል።

ግብፅ ከሱዳን መከላከያ ሠራዊት ጋር ስምምነት መፈጸሟንና የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን የሱዳን ህዝብ እያወገዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ ሱዳንን ወደ ጦርነት የምትገፋት የህዳሴው ግድብን መጠናቀቅ ተከትሎ ኢትዮጵያ በቀጣናው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ትይዛለች ከሚል ስጋት እንደሆነም ሱዳናዊ የሚዲያ ባለሙያና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኙ ማስታወቃቸውን ኢዜአ አዲስ ዘመን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!