Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዕቁብ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)እቁብን ለማዘመን ታልሞ በእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ የተሰራው መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ይፋ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አንዷ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሃና ኤርሚያስ እንደገለፁት መተግበሪያው በአካል ዕቁብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመስሎና የበለጠ ተጠያቂነት፣ የአጠቃቀም ቅለት እንዲሁም እቁቦቹ በሌሎች ሰዎች ይበልጥ እንዲገኙ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡
የእቁብ መተግበሪያው እንደ ማስታወሻ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ የክፍያ ስርዓቶች እና የመረጃ ጥንቅሮች ያሉ አዳዲስ ገፅታዎችን በመጨመር ለተጠቃሚ ምቹ ሆኖ የመጣ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልፀዋል፡፡
መተግበሪያው በእቁብተኞቹ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ገፅታዎችንም የያዘ ሲሆን በሌላ መልኩ የመተግበሪያ ተጠቃሚዎች በተለያየ ጊዜ የሚያሳዩትን ምግባር በመከታተል ነጥብ መስጠት እና የእቁብ አስተዳዳሪዎችም ይህን ነጥብ እንዲመለከቱ በማድረግ ወደ እቁባቸው ማን መቀላቀል ይችላል አይችልም የሚለውን ለመወሰን የሚረዳ ገጽታንም ይዟል፡፡
መተግበሪያው እቁቡ ስለተጣለባቸው ዙሮች እንዲሁም እቁቡን ሳይጥሉ ያሳለፉ እቁብተኞች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከሳምንት በፊት በጉግል አፕ ስቶር ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው መተግበሪያው በእስካሁኑ ቆይታው ከ500 ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ለመደረግ (ለመውረድ) የበቃ ሲሆን መተግበሪያው ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ባሉት ቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥም 30 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ ማለሙን ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version