አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራናውያን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን በኢራን ወታደራዊ ጦር ተመቶ መውደቁን ተከትሎ በመንግስት ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ነው።
የሀገሪቱ ጦር ባለፈው ቅዳሜ አውሮፕላኑን በተፈጠረ ስህተት መቶ መጣሉን ማመኑ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የሃገሬው ዜጎች በመንግስታቸው ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ከቴህራን ዩኒቨርሲቲ ውጭ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ዜጎች መንግስትን ጠላታችሁ አሜሪካ ናት እያለ ይዋሸናል፤ ጠላታችን ግን እዚሁ ይገኛል ብለዋል።
ሌሎች ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ከሌላኛው ዩኒቨርሲቲ ውጭ በመሆን እና ወደ ቴህራን አዛዲ (የነፃነት) አደባባይ በማቅናት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደነበረ ተጠቁሟል።
ተቃዋሚዎቹ በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን ውድቀት ለአምባገነኑ አስተዳደር የሚሉ እና ፀረ መንግስት መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበረ ነው የተነገረው።
ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ለመበትን ጥረት ማድረጉ ነው የተነገረው።
176 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው የዩክሬን መንገደኞች አውሮፕላን ከቴህራን ከተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ መከስከሱ የሚታወስ ነው፡።
ይህንን ተከትሎ ካናዳን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ኢራን አውሮፕላኑን መታ መጣሏን የሚያሳይ መረጃ አለን ሲሉ ኢራን በበኩሏ ሁኔታን ስታስተባብል ቆይታለች።
ሆኖም ከቀናት በኋላ የሀገሪቱ ጦር የዩክሬን መንገደኞች አውሮፕላንን በስህተት በሚሳኤል መቶ መጣሉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በሀገሪቱ መንግስት ላይ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ምንጭ፡- ሚዲል ኢስት ሞኒተር