Facebook logo and Australian flag are displayed in this illustration taken, February 18, 2021. REUTERS/Dado Ruvic/Illustration

ቴክ

ፌስቡክ ከሶስት የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ጋር ለሚያጋሩት ዜና ገንዘብ ለመክፈል ተስማማ

By Meseret Awoke

February 26, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ፌስቡክ ከሦስት የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ጋር በገጹ ላይ ለሚያጋሩት ዜና ገንዘብ መክፈል የሚያስገድደውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የአውስትራሊያ ፓርላማ እንደፌስቡክ ያሉ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ ለሚያጋሩት ዜና ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያደርግ ህግ አጽድቋል፡፡

ይህን ተከትሎም የፌስቡክ ኩባንያ ከሶስት የአውስትራሊያ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋር ስምምነቶችን ፈርሟል፡፡

ስምምነቱ የሚዲያ አውታሮቹ በገጻቸው ለሚያጋሩት ዜና ፌስ ቡክ ገንዘብ እንዲከፍል የሚያደርገው ነው፡፡

ፌስቡክ የአውስትራሊያ ተጠቃሚዎች ዜና እንዳይመለከቱ ወይም እንዳያጋሩ ከሳምንት በፊት እግድ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ኩባንያው እገዳውን አንስቶ ስምምነቱን መቀበል ግድ ሆኖበታል፡፡

አውስትራሊያ ያወጣችውን ድንጋጌ ሲኮንን እና ሲቃወም የነበረው የመረጃ ማፈላለጊያው ገጽ ጎግል የተባለውን ክፍያ ለመክፈል መስማማቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ፌስቡክም የሃገሪቱን ህግ በመቀበል ስምምነት ፈጽሟል፡፡

በዚህም ሃገሪቱ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ ለሚያጋሩት ዜና ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ቀዳሚ ሆናለች፡፡

ሆኖም የስምምነቱ የፋይናንስ ዝርዝር ግልጽ አለመደረጉን መረጃው አንስቷል፡፡

ምንጭ፡- አልጀዚራ