አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የገጠር ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ኤግዚቪቢሽን በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በኤግቪቢሽኑ ላይ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስተር ዶክተር ሂሩት ካሣው፣ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኦርጌሳ እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ካባ ኦርጌሳ፥ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች በገጠር ስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ4 ነጥብ 1ሚሊየን ወይም 87 በመቶ የስራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
የስራ ዕድሉ የተፈጠርው በግብርና፣ በማዕድን፣ በማምረቻ እና ንግድ ዘርፎች እንዲሁም በመንግስት ትልልቅ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች መሆኑን ሚኒስተር ዴኤታው ገልፀዋል።
በየዓመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም በመግለፅ፤ ከስራ ፈላጊዎች ብዛት አኳያ ሲታይ ገና በጅምር ላይ በመሆኑ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።
ከዚህ በመነሳት ለስራ ፈላጊ ዜጎች በተለይ ለወጣቶችና ለሴቶች የአካባቢውን የልማት ፀጋ በመለየትና በመጠቀም የስራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማርጋገጥ ከክልሎችና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ጠቁርጠኝነትና በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ዶክተር ካባ ገልፀዋል።
የገጠር ኢንተርፕራይዞች ላመረቱት ምርት የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው የገበያ ትስስር የማጠናከር ስራዎች ላይ በትኩርት እየተሠራ መሆኑን ሚኒስተር ደኤታው ተቁመዋል።
በኤግዚሽኑ የጅማ ቡና እና ማር፣ የአላባ በርበሬ እንዲሁም ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የግብር ምርቶች እና የጎንደር ጃኖ ቀርቧል።
በናትናኤል ጥጋቡ