Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትግራይ ክልል ከ75 በላይ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ለማድረግ በአሁኑ ሰአት ከ75 በላይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም በሳምንቱ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ በሀገራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በዜጋ ተኮር የዲኘሎማሲ ስራዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በአፋጣኝ ለመድረስ በክልሉ 36 ወረዳዎች በተቋቋሙ 92 የእርዳታ ማሰራጫ ጣቢያዎች በኩል ድጋፍ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቱርክ አንካራ እና በህንድ ኒውደልሂ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን ጥብቅ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስር የበለጠ ለማሳደግ እና በጋራ ለመስራት የሚያስችል መግባባት ላይ ደርሳለችም ብለዋል ቃልአቀባዩ፡፡

የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይናው አቻቸው ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ አቶ ደመቀ በዚሁ ወቅት የትግራይ ጉዳይ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን እንደሚያራግቡት አለመሆኑን እና መንግስት አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

በዜጋ ተኮር ዲኘሎማሲም ከየካቲት 8 እስከ 22 ከጅዳ እና ሪያድ 699 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አውስተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version