አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል-10 ቢሮ እየተከናወነ ባለው የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ምልከታ አደረገ።
የምርጫ ክልሉን የሥራ ሂደት ለመፈተሽ ምልከታ ያደረጉት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ እና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ ሶሊያና ሽመልስ ናቸው።
የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ ሶሊያና ሽመልስ አዲስ አበባ የዕጩዎች መመዝገቢያ ክልሎችን ቢሮ ካሟሉ አስተዳደሮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመዲናዋ የሚገኙት 33 የምርጫ ክልሎች ከየካቲት 8 ቀን 2013 ጀምሮ ቢሮዎቻቸውን አመቻችተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የዕጩዎች መመዝገቢያ ክልል-10 ቢሮ ዛሬ አራት ዕጩዎችን መመዝገቡን በምልክታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ያልተመዘገቡ የፓርቲና የግል ዕጩዎችም የፊርማ ማሰባሰቢያ ቅፅ ወስደው በመሙላት እየተመዘገቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዕጩዎች ምዝገባ በዚህ ሳምንት መጀመሩን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤ በሚቀጥለው ሳምንት የዕጩ ተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።
የምርጫ ምዝገባ ያልተጀመረባቸው የዕጩ መመዝገቢያ ቢሮዎች ምዝገባ የሚያካሂዱበት ቀነ-ገደብ በቦርዱ እንደተቀመጠም ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ባህርዳር፣ ሃዋሳ እና ጎዴን ጨምሮ በሌሎች 12 ከተሞች ለምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንና እንደተጠናቀቀም በቀሩት የምርጫ ክልሎች የዕጩ ምዝገባ እንደሚጀመር አስረድተዋል።
የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት መዘግየትና ሌሎች ጥቃቅን ችግሮች ለቦርዱ የቀረቡ ቅሬታዎች እንደነበሩ አስታውሰው÷ ቁሳቁሱን በፍጥነት ማቅረብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የዕጩዎች ምዝገባ በወረቀት ከተሞላ በኋላ ማህተም ተደርጎበት ጎን ለጎን ወደ ሰርቨር እየገባ መሆኑ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ሂደትን በማፋጠን ስራ ለማቃለል እንደሚረዳ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!