አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ላለፉት አመታት ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር የቴክኒክ ውይይት ስታደርግ የቆየችው ግብፅ አሁንም ፖለቲካዊ መፍትሄን መርጣለች።
ግብፅ የአባይ ወንዝ መነሻዋ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ባይተዋር ሆና እንድትኖር ትሻለች፤ ይህም ከህዳሴው ግድብ ግንባታ በፊትም ሆነ በኋላ የታየ ሲሆን በትናንትናው እለትም ይህንኑ የሚያጠናክር ሀሳቧ በአዲስ አበባ ተደምጧል።
የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተካፈሉበትን 4ኛ ዙር የቴክኒክ ውይይት ሲያጠናቅቁ ከግብፅ የቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች ውይይቱ ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።
በቴክኒክ ውይይቶቹ ላይ ለረጅም ጊዜ የተካፈሉት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ግብፅ ኢትዮጵያ አቅርባው በነበረው ከ4 እስከ 7 አመት ግድቡ ይሞላ ሀሳብ ለመቀበል ተለሳልሳ እንደነበር ተናግረዋል።
ትናንት ግን አዲስ ጥናት አስጠናን በሚል ግድቡ ከ12 እስከ 21 አመት ባለው ጊዜ ነው መሞላት ያለበት ብለዋል ነው ያሉት።
ይህ አዲስ የግብፅ የሙሌት ሀሳብ በግድቡ ግንባታ ላይ ጫናን ባያሳድርም፤ ኢትዮጵያን በታዛቢዎቹ ፊት በማሳጣት ወደ መስመር ለማስገባት ከመነጨ ፍላጎት ሊሆን እንደሚችልም ነው ዶክተር ያዕቆብ የሚጠቁሙት።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ ደግሞ ይህ የካይሮ አካሄድ የተፈለገውን ውጤት ያመጣላቸዋል ወይ የሚለውን ጉዳይ አጠያያቂ አድርጎታል ባይ ናቸው።
በየጊዜው አቋምን መለዋወጥ በዲፕሎማሲው መስክ የሽንፈት ማሳያ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ በአንፃሩ በግድቡ ላይ የሰራችው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስራ በዲፕሎማሲው ስኬት አምጥቶላታል የሚሉት አቶ እንዳለ፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸውን ተግባራት እየተረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
ግብፅ ስጋቷን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ጭምር በማሰለፍ ብትሰራም የግድቡ ግንባታ ከ65 በመቶ በላይ መድረሱንም የስኬቱ ማሳያ አድርገውታል።
እኛ ብቻ እንጠቀም የሚል ድምፅ የምታስተጋባው ግብፅ ግን አሁንም የአባይን ጉዳይ ከውሃ ፍላጎት አንፃር ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ማቀዝቀዣዋ ማድረጓን ቀጥላበታለችም ነው ያሉት።
ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የአስዋን ግድብን የውሃ መጠን እንዳይጎዳ የውሃ አሞላሉ እንዲሁም አለቀቃቁ ላይ ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎችም አሉ።
የተፈጥሮ ፍሰት በሚል ግብፅ የምታቀርበው ሀሳብ በቃል እና በፅሁፍ የተለያየ ሲሆን፥ ግድቡ ከእነጭራሹ ለምን አስፈለገ የሚያስብል መሆኑንም ዶክተር ያዕቆብ ያብራራሉ።
ድርቅ ቢከሰት የውሃ አያያዙ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጉዳይ ላይም ሀገራቱ ያስቀመጡት አሃዝ ወደ አማካዩ መቀራረብ የሚያስችል ቢሆንም ግብፅ ለዚህ ፈቃደኛ አልነበረችም ተብሏል።
የሶስትዮሽ የቴክኒክ ውይይቱ ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የሀገራቱ ልዩነት በ2015 በካርቱም በተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል።
የመርህ ስምምነቱ አንቀፅ 10 ሀገራቱ መግባባት ካልቻሉ በአሸማጋይ ይነጋገሩ ወይም ለሀገራቱ መሪዎች አሳውቀው መፍትሄ እንዲበጅለት ይደነግጋል።
ሶስተኛ ወገን እንዲገባ ስትወተውት የቆየችው ግብጽ አሁን ይህን እድል ለመጠቀም የቋመጠች ቢመስልም፥ ስምምነቱ በሶስቱ ሀገራት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው ዶክተር ያዕቆብ የሚገልጹት።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እንዳለም በቴክኒክ ያልተግባቡትን በፖለቲካዊ አካሄድ ይፈታል ብሎ ማመኑ የሚያዋጣ አይመስልም ብለዋል፤ ወደ ድርድር ቢመጡ መነሻቸው የቴክኒክ ግኝቱ መሆኑን በመጥቀስ።
ግብፅ በ4ኛው ዙር ስብሰባ ይዛ የመጣችው አዲስ ሀሳብ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ አለመሆኗን በግልፅ ያሳየ እንደነበር የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።
የግብፁ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሙሀመድ አብዱል አቲ ግን በብዙ ነገር ላይ ግልፅ አረዳድ አለ፤ በዋሽንግተንም ስምምነት ላይ እንደርሳለን ማለታቸው አነጋጋሪ ነበር። ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው በዋሽንግተን ምንም አይነት ድርድር ወይም ስምምነት እንደማይኖር አንስተዋል።
የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውሃ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሰኞ እና ማክሰኞ በዋሽንግተን በሚኖራቸው ቆይታ፥ በእስካሁኑ የድርድር ሁኔታ ዙሪያ ለዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ሀላፊ ገለፃ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፋሲካው ታደሰ