አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውሃ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር የሀይል አቅርቦቱን በአራት እጥፍ ማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ገለፀ።
ኢትዮጵያ በውሀ ሀብቷ ከ40 እስከ 50 ሺህ ሜጋ ዋት ያክል የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት እና የማምረት አቅም እንዳላት ይታመናል።
ይሁን እንጅ ከውሃም ይሁን ከሌሎች ታዳሽ የሀይል ምንጮች የሚመረተው የሀይል መጠን ከ4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት መሻገር አልቻለም።
ይህን ተከትሎም እየጨመረ የመጣውን የሀይል ፍላጎት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እና የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦችን ያካተተ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የውሃ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፍኖተ ካርታው አቅምን ያገናዘበ ፍትሀዊ የአገልግሎት ተጠቃሚነትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም አጠቃላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማፋጠን የሚያስችሉ አላማዎችን የያዘ ነው።
ከዚህ ባለፈም የሀይል ምርትን በአግባቡ ማምረትና ያለምንም የመሰረተ ልማት ችግር ለህብረተሰቡ ማዳረስ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
የትራንስፎርመሮችን እና የቆጣሪ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሀና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የሃይል አማራጮችን ከማስፋት ባለፈም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅቶ የመስራት ባህልን እንደሚያዳብርም ጠቁመዋል።
በፍኖተ ካርታው አሁን ያለውን የኤሌክትሪክ መስመር ከ20 ሺህ ወደ 34 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚያድግ መሆኑም ተጠቅሷል።
እንዲሁም የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ከ204 ወደ 256 የሚያሳድግ እና ሁሉም ዜጋ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል።
የሚመረተው የሀይል መጠንም ወደ 20 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያድግ ሲሆን፥ ከውሃ 14 ሺህ፣ ከፀሃይ ሀይል 1 ሺህ 700፣ ከእንፋሎት 900 ሜጋ እንዲሁም ከነፋስ እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የሚደርስ ሀይል እንደሚመረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
በሙሀመድ አሊ