ቴክ

ፌስቡክ የአውስትራሊያ ተጠቃሚዎችን ዜና እንዳይመለከቱ ወይም እንዳያጋሩ አገደ

By Meseret Awoke

February 18, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌስቡክ ኩባንያ የአውስትራሊያ ተጠቃሚዎች ዜና እንዳይመለከቱ ወይም እንዳያጋሩ ማገዱ ተገለጸ፡፡

አውስትራሊያ የዛሬ ወር አካባቢ እንደ ጎግል እና ፌስ ቡክ ያሉ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የሚዲያ አውታሮችን ጨምሮ ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ ለሚያጋሩት ዜና ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያደርግ ድንጋጌ ማውጣቷ ይታወሳል፡፡

ድንጋጌውን ተከትሎም ኩባንያዎቹ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፤ አካሄዱም አግባብ አይደለም በሚልም ተችተውታል፡፡

የአሁኑ እገዳም በሃገሪቱ ለወጣው ድንጋጌ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡

አውስትራሊያውያንም ከዛሬ ጀምሮ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገር የሚዲያ አውታሮችን መረጃዎች በገጻቸው ማግኘት አልቻሉም ነው የተባለው፡፡

ከሃገሪቱ ውጭ የሚገኙትም ቢሆን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የአውስትራሊያ የዜና አውታሮችን መረጃ በፌስ ቡክ ገጻቸው ማንበብ ወይም መድረስ አይችሉም ነው የተባለው ፡፡

የአውስትራሊያ መንግስትም የፌስቡክን እርምጃን አጥብቆ ተችቷል፡፡

አውስትራሊያ ያወጣችውን ድንጋጌ ሲኮንን እና ሲቃወም የነበረው የመረጃ ማፈላለጊያው ገጽ ጎግል የተባለውን ክፍያ ለመክፈል መስማማቱ ታውቋል፡፡

ወደ 17 ሚሊየን የሚሆኑ አውስትራሊያውያን በየወሩ ማህበራዊ ሚዲያውን እንደሚጎበኙ መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ