ጤና

ጥሩ እንቅልፍ እንዳያገኙ የሚያደርጉ ምክንያቶች

By Tibebu Kebede

January 10, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሁኔታዎች ለእንቅልፍ መቆራረጥ ምክንያት መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ሰዎች ከተኙ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ይነቃሉ፤ የየዕለት ውሎ፣ አመጋገብ፣ ጭንቀትና መሰል ጉዳዮች ለዚህ ምክንያት ይሆናሉ።

ባለሙያዎች ደግሞ ጥሩ እንቅልፍ እንዳይኖር የሚያደርጉ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል

የሰውነት ሙቀት፦ በመኝታ ሰዓት ሰውነት ከፍተኛ ሙቀት የሚያመነጭ ከሆነ በተደጋጋሚ ለመንቃት ይገደዳሉ።

ባለሙያዎቹም በመኝታ ሰዓት የሰውነት ሙቀታቸው ቀዝቃዛ የሆኑ ሰዎች ለእንቅልፍ መቆራረጥ እንደማይዳረጉ ይገልጻሉ።

የቀን ውሎ አጋጣሚዎች፦ በቀን ውሎዎ የተከሰተ አሳሳቢ ክስተት፣ ያልታሰበ ክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ከአዕምሮ የማይጠፉ መጥፎ አጋጣሚዎች ጭንቀትን በማስከተል በቂ እንቅልፍ እንዳይተኙ ያደርግዎታል።

ለዚህ ደግሞ ራስን ማረጋጋትና ነገሮችን አለማስታወስ መፍትሄ መሆኑን ይመክራሉ።

የአልኮል መጠጦች፦ የአልኮል መጠጥ በፍጥነት እንቅልፍ እንዲተኙ ቢረዳዎትም ሌሊት ላይ እንቅልፍን በመረበሽ የቀን ውሎና ስራ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡

አነቃቂ ነገሮች፦ ቡናን ጨምሮ አነቃቂ መጠጦችን በእንቅልፍ ሰዓት መውሰድም ለእንቅልፍ እጦት ሌላኛው ምክንያት ነው።

በመኝታ ሰዓት አነቃቂ መጠጦችን መውሰድ፥ የመቁነጥነጥና ያለመረጋጋት፣ ለሆድ መነፋት፣ በተደጋጋሚ ለሽንት እንዲነቁ በማድረግና የልብ ምት ፍጥነትን በመጨመር ለእንቅልፍ እጦት ይዳርጋል።

ማንኮራፋት፣ በቀን ውሎዎ ያጋጠመዎት ከፍተኛ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የስሜት መቀያየርና መጥፎ አጋጣሚዎችን ወይም ችግሮች ላይ ብቻ የበዛ ትኩረት ማድረግም ሌላው የእንቅልፍ እጦት መንስኤ ነው።

አመጋገብ፦ ከመኝታ በፊት የቅባት እና ካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያሉ ከባድ ምግቦችን ያስወግዱ።

ጭንቀትና ድብርት፦ አእምሮን እረፍት በመንሳት በቂና ጤናማ እንቅልፍ እንዳያገኙ መንስኤ ይሆናል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ በመኝታ ሰዓት አቅራቢያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግን የህክምና ባለሙያዎች አይመክሩም።

የስልክ አጠቃቀም፦ በመኝታ ሰዓት ሞባይል ስልኮችን መጠቀም ከስክሪኑ የሚወጣው ጨረር አዕምሮን እንዲጨናነቅና እንዲነቃ ስለሚያደርገው ለእንቅልዕፍ እጦት ይዳርጋል።

ከዚህ አንጻርም ከመኝታ ከአንድ ሰዓት በፊት ከእጅ ስልክዎ ጋር ቢለያዩ ይመከራል።

ረዘም ላለ ጊዜ የሚኖር የሸለብታ ጊዜ፦ በስራ ሰዓት ድካም ሲሰማ የተወሰነ ደቂቃ ሸለብታ መውሰድ ድካምን ለመቀነስ እጅጉን ይረዳል።

ይሁን እንጅ ረዘም ላለ ጊዜ ሸለብታ ማድረግ በምሽቱ የመኝታ ሰዓት ለእንቅልፍ እጦት የሚዳርግ በመሆኑ ያንን ያስወግዱ።

ምንጭ፡- psychologytoday.com