አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሩሲያ እና ቱርክ በሶሪያ ኢድሊብ ግዛት የተኩስ አቁም ስምምነት መድረሳቸውን አስታወቁ።
ስምምነቱ የሶሪያ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ለማስቆም እና በአካባቢው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያለመ ነው ተብሏል።
ዛሬ የሚጀምረው የተኩስ አቁም ስምምነት ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ ግን የተባለ ነገር የለም።
ቱርክ ባለፈው ወር በኢድሊብ ግዛት የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረስ ዘንድ ሩሲያን ጠይቃ ነበር።
በወቅቱ ሩሲያ እና የመንግስት ሃይሎች በአማጽያን ይዞታ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል።
በሶሪያ የአማጽያን የመጨረሻ ይዞታ የሆነችውን ኢድሊብ ለማስለቀቅ የበሽር አላሳድ ወታደሮች ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛል።
ይህ ደግሞ ለንጹሃን ህልፈትና በአካባቢው ለሚደርሰው ማህበራዊ ቀውስ ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
በአካባቢው ያለውን ግጭት ተከትሎ በታህሳስ ወር ብቻ 300 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከኢድሊብ ወደ ቱርክ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
የሶሪያ ቀውስ ከጀመረበት የፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ከ370 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2019 ደግሞ ከ1 ሺህ የሚበልጡ ህጻናትን ጨምሮ 11 ሺህ 215 ሰዎች በጦርነቱ ሳቢያ ህይዎታቸው አልፏል።
ምንጭ፦ አልጀዚራ