አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኒጀር ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 25 ወታደሮች መገደላቸው ተሰማ።
ጥቃቱ በማሊ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፥ ከሞቱት በተጨማሪ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።
ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም፥ ከአል ቃይዳ እና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂዎች ሳይፈጽሙት እንዳልቀረ ነው የተነገረው።
ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ 63 ታጣቂዎች መገደላቸውም ተገልጿል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ አክራሪ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበትና ለመንግስት ወታደሮች አስቸጋሪ ስፍራ መሆኑ ይነገራል።
ምንጭ፡-ሲ ጂ ቲ ኤን