Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ማላዊ የኢትዮጵያን አጋርነት እንደምትፈልግ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማላዊ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፒተር ሙታሪካ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሳደግ እንደምትፈልግ ተናገሩ።

ፕሮፌሰር ሙታሪካ መቀመጫቸውን ናይሮቢ በማድረግ በማላዊ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን በመሆን የተሾሙትን አምባሳደር መለስ ዓለምን የሹመት ደብዳቤ በብሔራዊ ቤተመንግስት ተቀብለዋል።

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ማላዊ በተቋማት እና በህዝቦች መካከል ትስስር እንዲኖር መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ወደ ማላዊ በሳምንት ሰባት ጊዜ የሚበረው እና ከማላዊ አየር መንገድ ጋር በሽርክና የሚሰራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለቱን ሃገራት በንግድ እና ቱሪዝም እንዲተሳሰሩ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

አምባሳደር መለስ በበኩላቸው፥ የሃገራቱን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እና ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ማላዊ በተለያየ መልክአ ምድር ቢኖሩም በዓለም አቀፍ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ሲተባበሩ የቆዩና ይህንኑ ማጠናከር ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version