Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያተኮረ የኢትዮ ህንድ የቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ትኩረቱን በኢትዮጵያ በሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያደረገ የኢትዮ ህንድ የቢዝነስ ፎረም በህንድ ኒው ደልሂ ተካሄደ፡፡

ፎረሙን በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከህንዱ የመጽሄት አታሚ ኩባንያ ጋር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፥ በፋርማሲዩቲካልስ፣ ማዕድን፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በግንባታ እና በኬሚካል ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ ከ30 በላይ የህንድ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፡፡

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ ፎረሙ የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲገነዘቡ ከማስቻል አንጻር ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የአየር ንብረት፣ የሰው ሃይል እና ርካሽ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ሃገሪቱን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታልም ነው ያሉት፡፡

በዚህ ወቅትም መንግስት በኢትዮጵያ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ምቹ የስራ ድባብ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በማብራሪያቸው መንግስት ኢትዮጵያን በአፍሪካ የማምረቻው ዘርፍ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ፥ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ሰፊ ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡

በፎረሙ ወቅት ለህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አቅም፣ ምቹ ሁኔታዎች፣ በመንግስት ስለሚደረጉ ማበረታቻዎች እና ስለ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version