አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ በዛሬው እለት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ።
ከምዕራብ አባያ ወረዳ ወደ አርባምንጭ ከተማ ሲጓዝ የነበረ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ/ሚኒ ባስ ተሽከርካሪ መኪና ላይ ዛሬ ጥዋት 2:30 አከባቢ በደረሠ የመገልበጥ አደጋ ነው የሰው ህይወት ያለፈው።
በደረሰው የትራፊክ አደጋም የ4 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ16 ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ እንዲሁም በ3 ሰዎች ላይ ደግሞ ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ረታ ተክሉ ገልፀዋል።
የአደጋው መንስኤ ከተፈቀደው የወንበር ቁጥር በላይ መጫን እና ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑንም መግለፃቸውን በጋሞ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በአደጋው የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ በወላይታ ሪፌራል ሆስፒታል እንዲሁም ሌሎቹ በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።