አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከቁርስ በፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የስብ ክምችትን ለማቃጠል እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመላከተ።
በብሪታንያ የተደረገው ጥናት ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በፊት ቁርስ የሚመገቡ እና ሳይመገቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሁለት ቡድኖችን አካቷል።
በጥናቱ ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጡ 30 ሰዎች ለስድስት ሳምንታት በተደረገው ሙከራ ተሳትፈዋል።
በዚህም ቁርሳቸውን ሳይመገቡ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ተመግበው ከሚሰሩ ሰዎች ሁለት እጥፍ የስብ ክምችትን ማስወገድ መቻላቸው ተገልጿል።
ሳይመገቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሰውነት ያጠራቀመውን ምግብ በተለይም ከፍተኛ የስብ ክምችትን እንዲያቃጥል እንደሚረዳውም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም በደም ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የስኳር መጠን የሚቆጣጠረው ኢንሱሊን በአግባቡ ስራውን እንዲሰራ እንደሚያግዘው አስረድተዋል።
ይህም የስኳር በሽታን እና የልብ ህመም ችግርን ለመከላከል ያግዛልም ነው ያሉት።
ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ሳይመገቡ የሚሰሩት ተመግበው ከሚሰሩት ባነሰ መልኩ ክብደት መቀነሳቸውንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2010 በተደረገ ጥናት ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቷል።
በጥናቱ ሁለት ቡድኖች የተለዩ ሲሆን፥ የአንደኛው ቡድን አባላት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚያዘወትሩ ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ምንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያላደረጉትና ምግብ ተመግበው የሰሩት ክብደታቸው ሲጨምር፥ ምግብ ሳይመገቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ክብደት በመቀነስ የስብ ክምችታቸውን ማቃጠል መቻላቸው ተገልጿል።
ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን