የሀገር ውስጥ ዜና

የገመድ ላይ ተሽከርካሪን ጨምሮ አዳዲስ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው – ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ

By Tibebu Kebede

February 01, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የገመድ ላይ ተሽከርካሪን ጨምሮ አዳዲስ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚዘጋጀውና ትኩረቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ካደረገው “ፖሊሲ ማተርስ” የውይይት መድረክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሃገሪቱን የትራንስፖርት ፖሊስ ማርቀቅ ቀዳሚው መሆኑን በመጥቀስም፥ ፖሊሲው የገመድ ላይ ተሽከርካሪን ጨምሮ አዳዲስና ዘመናዊ የትራንስፖርት አማራጮችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያ የሆነው የትራንስፖርት ፖሊሲ ዘርፉን እንዴት ማዘመን እንደሚቻል ግልጽ መመሪያን የያዘ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም በዘርፉ ከሎጅስቲክስ ጋር በተያያዘ ያለውን አሰራር ማሻሻል ያለመ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ መፅደቁንም አውስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለእግረኞችና ለአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ቅድሚያ የሚሰጠው የሞተር አልባ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስትራቴጅ መፅደቁንም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሯ በቆይታቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ከሃገር ውስጥ ባለፈ ለጎረቤት ሃገራት የሎጂስቲክስ ማዕከል የመሆን እቅድ እንዳላትም ነው የተናገሩት፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!