ውድድሩ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ የቦታ ለውጥ አድርጎ በሱልልታ ከተማ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ እንደተናገረው፤ በሩጫው እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው አገሮች መካከል የኬንያ፣ ሱዳንና፣ ደቡብ ሱዳን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
የየአገሮቹ አትሌቶች በነገው እለት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጃንሜዳ በጊዜያዊነት የአትክልት መሸጫ ቦታ ሆኖ በመቆየቱ ለሩጫው ቦታ የማስተካከል ስራ የተወሰነ ጊዜ ስለሚወስድ የዘንድሮ ውድድር በሱልልታ እንደሚካሄድ አትሌት ገዛኸኝ ገልጿል።
ውድድሩ በ10 ኪሎ ሜትር በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ በስምንት ኪሎ ሜትር በወጣት ወንዶች፣ በስድስት ኪሎ ሜትር በወጣት ሴቶች፣ በስምንት ኪሎ ሜትር ድብልቅ ሪሌና በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ መሆኑን የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ገልጸዋል።
በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች እንደ ደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
“በግል በሚደረገው የአዋቂ ወንዶችና ሴቶች ውድድር ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለሚያጠናቅቁ ለእያንዳንዳቸው ከ40 ሺህ ብር እስከ 6 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ይሰጣል” ብለዋል።
በወጣት ወንዶችና ሴቶችም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁም ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሺህ እስከ 4 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በድብልቅ ሪሌና ለአንጋፋ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።
እንደኢዜአ ዘገባ በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ ከገንዝብ ሽልማቱ በተጨማሪ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ይሰጣቸዋል።
ውድድሩ ኮቪድ-19 መከላከያ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ የሚካሄድ እንደሆነና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉ ነው የተገለጸው።
በዚህ ሻምፒዮና አሸናፊ አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ከወር በኋላ በቶጎ በሚካሄድ የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ይሆናል።
በ38ኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ከ800 በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!