Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ከቱርክ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ ከቱርክ አምባሳደር ያፓራክ አለፐ ጋር ተወያዩ፡፡

አቶ አደም ፋራህ መንግስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለአምባሳደር ያፓራክ አለፐ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስድስተኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫን በተመለከተ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምክር ቤቱ ከሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት እንዲራዘም መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረት ውሳኔውን ተከትሎ ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነውን ሕገ መንግስታዊ ውሳኔ አክብረው ተፈጻሚ ያደረጉ ሲሆን፥ የህወሓት አመራሮች ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሚጻረር መንገድ የክልል የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ሕገ ወጥ ምርጫ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሕገ ወጡ የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እጅግ አስነዋሪ ጥቃትና የሀገር ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ተገዶ ወደ ሕግ ማስከበሩ ዘመቻ መግባቱንም አፈ ጉባኤው አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ዘመቻው ተጠናቆ ወንጀለኞችን የማደን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችንና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ እና ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፎችን የማቅረብ ሥራን የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሕዝብን በማስተባበር ስራ እየሰራ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡

ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም በቀጣይ ከቱርክ መንግስትና ሕዝብ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው የቱርክ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ እያደረገ ላለው ሁሉ አቀፍ ድጋፉና ትብብር አመስግነዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፓራክ አለፐ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን አድንቀው ለስኬታማነቱ የቱርክ መንግስት የልማት ድጋፍና ትብብር እንደማይለየው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቱርክ ባለሃብቶችን በመሳብ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ ሃገራት ያለው የንግድና የምጣኔ ሀብት ግንኙነት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስም የሃገራቸው ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፉ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version