አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንሳይ ፓሪስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ቡና ማስተዋወቂያ ፎረም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፅዮን ተክሉ፥ የኢትዮጵያ ባለልዩ ጣዕም ቡና ዋና ዋና ባህሪያትን፣ የቡና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን፣ ከገበያ አንፃር የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻዎችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እና የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የቡና ንግድን ለማሳደግ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ለተሳታፊዎቹ አረጋግጠዋል ፡፡
ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡናን ያበረከተች ታሪካዊት ሀገር መሆኗን በመጥቀስ፥ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ “ምድረ ቀደምት” የሚል መጠሪያ በትክክል የሚገልፃት እና በዚሁ ስም በመጠቀም ፀጋዎቿን ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ መሆኗን ገልፀዋል።
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በበኩላቸው አብዛኛው የቡና ንግድ ሥራ የሚካሄደው በደላሎች አማካኝነት መሆኑን ጠቁመው፥ የቡና ንግዱ በቀጥታ በአስመጪዎና ላኪዎች መካከል የሚካሄድበትን መንገድ መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አምባሳደሩ በመዳረሻ ገበያዎች የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማመልከትም፥ በቡና ንግድን ዘርፍ ተሳታፊ ለሆኑት አካላት የተጠናከረ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በፎረሙ ላይ ከ53 በላይ የቡና ዘርፍ ቁልፍ ተዋንያን መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!