ኢራን ለ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት እንደማትገዛ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን በፈረንጆቹ 2015 የኒውክሌር ስምምነት ላይ የተጣለውን ማንኛውንም እገዳ እንደማታከብር አስታውቃለች።
ቴህራን በስምምነቱ ላይ ያላትን አቋም በገለጸችበት መግለጫ በምታበለጽገው ኒውክሌር መጠን ላይ ቅነሳ እንደማታደርግና ኒውክሌርን ለምርምርና ልማት መጠቀሟን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
ኢራን በስምምነቱ የተጣለውን እገዳ አላከብርም ትበል እንጅ አሁንም ቢሆን ለድርድር በሯ ክፍት መሆኑን ገልጻለች።
በፈረንጆቹ 2015 የተደረሰው ስምምነት ኢራን በምታበለጽገው የኒውክሌር መጠን ላይ ገደብ የጣለ ነበር።
ከኢራን አቋም ጋር ተያይዞም የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን ጨምሮ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ኢራን ስምምነቱን ከሚጥስ እርምጃዋ እንድትታቀብ ጥሪ አቅርበዋል።
ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቻይና እና ሩሲያ ከኢራን ጋር በስምምነቱ የቀሩ ሃገራት ሲሆኑ፥ አሜሪካ ባለፈው አመት ከስምምነቱ መውጣቷ ይታወሳል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ