አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የፀጥታ ችግር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአንበጣ መንጋ ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎችም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱባቸውን ስፍራዎች ለማቋቋም የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ህብረተሰቡ ለአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ እርዳታ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ባቀረበው የእርዳታ ጥሪ መሰረትም ግጭቶች፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎችም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ባጋጠሙባቸው ስፍራዎች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ማህበሩ 300 የበጎ ፈቃደኞች እና ሠራተኞችን እንዲሁም 100 አምቡላንሶችን በማሰማራት በቅርቡ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ እና ከዚያ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ህይወት ለማዳን እና ኑሯቸውን መልሶ ለማቋቋም በንቃት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በታህሳስ 2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በምዕራብ ፣ ደቡብ እና መካከለኛው ትግራይ አካሄድኩ ባለው ወቅታዊ ግምገማ መሠረት በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በመተከል ዞን ፣ በኮንሶ እና ቤንቺ ሸኮ አካባቢዎች አጠቃላይ እና ተጨማሪ ምግብ የሚፈልጉ ከ 2 ነጥብ 53 ሚሊየን በላይ ተጋላጭ ሰዎች አሉ፡፡
ላለፉት ሁለት ወራት የተከሰቱትን የፀጥታ ችግሮች ተከትሎ በትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ኦሮሚያ በ30 ሚሊየን ብር ወጪ ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የህክምና፣ ምግብ፣ መጠለያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አቅርቦቶች፣ የስነ-ልቦና ማህበራዊ እና መልሶ የማቋቋም ቤተሰብ የማገናኘት አገልግሎቶችን ሲያከናውን መቆየቱንም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ተጨማሪ የጤና ማዕከል ተቋማትን እና የቀይ መስቀል ቅርንጫፎችን መጠገን እና መልሶ መገንባት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ለተጠቀሱ ስፍራዎች እርዳታም ከ9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
ስለሆነም በአይነት ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ የብሔራዊ ማኅበሩ ዋና መስሪያ ቤት እና በሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በገንዘብ የሰብአዊነት ድጋፍ ፈንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000 000 902 008 ፣ እንዲሁም በኦንላይን ልገሳ ለማድረግ የማህበሩ ሊንክ https://donate.bankofabyssinia.com/dashboard/ercs.php ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሷል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!