አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያዊው የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ፖል ቴርጋት በ20ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በክብር እንግድነት እንደሚገኝ ተገለጸ።
20ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ 20 ዓመት በሆነው የታላቁ ሩጫ ውድድር ታዋቂው
የኬንያ አትሌት ፖል ታርጌት በክብር እንግድነት እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
“እ.አ.አ 2000 በሲድኒ በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር ፖል ቴርጋት ከአትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ጋር ያደረጉት የመጨረሻ ሠዓት ትንቅንቅ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ነው” ብለዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱን ሲያከብር ፖል ቴርጋትን በክብር እንግድነት እንደጋበዘውና እሱም ግብዣውን ተቀብሎ በውድድሩ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ መስጠቱን ተናግረዋል።
ከፖል ቴርጋት በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው አንጋፋ የኢትዮጵያ አትሌቶችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በውድድሩ ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ የኬንያና የኤርትራ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ኤርሚያስ የጠቆሙት።
የ51 ዓመቱ ፖል ቴርጋት በመም፣ በአገር አቋራጭና በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ስኬታማ የውድድር ጊዜ የነበረው ነው።
እ.አ.አ 2000 በሲድኒ ኦሊምፒክ ውድድር የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ በሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በአንድ ማይክሮ ሴኮንድ ተቀድሞ የተሸነፈበት ውድድር ለአትሌቱም ሆነ ለአትሌቲክሱ ማኅበረሰብ የማይረሳ ታሪክ ነው።
ፖል ቴርጋት በውድድሩ በሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት የተሸነፈ ሲሆን ሃይሌ 27 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ19 ማይክሮ ሴኮንድ ሲያሸንፍ ኬንያዊው አትሌት 27 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ20 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል።