አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመሃል አዲስ አበባ ጎተራ አካባቢ የሚገነባው የአሚባራ መንደር ግንባታ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂር ታከለ ኡማን ጨምሮ፣ የኢፌዴሪ የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የአፋር ተወላጆችና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሩ በአፋር ባለሃብቶችና በከተማ አስተዳደሩ በጋራ የሚገነባ መሆኑ ተገልጿል።
መንደሩ የ35 ሺህ ካሬ ሜትር ነባር ይዞታቸው ላይ የከተማ አስተዳደሩ 15 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ በመጨመር በድምሩ በ50 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚገነባ ነው ተብሏል።
ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሩ በውስጡ ከ450 በላይ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ጨምሮ የገበያ ማዕከላት፣ ሆቴል፣ ተመራጭ የመዝናኛና የንግድ ማዕከል፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እና የአፋር ባህል ማዕከልን ያካተተ ነው።
ግንባታው በ11 ቢሊየን ብር የሚከናወን ሲሆን፥ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይነትም ሌሎች ባለሃብቶችን በማስተባበር መሠል ፕሮጀክቶችን እንደሚጀምር ተናግረዋል።
በአፋር ባለሃብቶች ለሚገነባው የአሚባራ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና በቻይና ኩባንያዎች ከሚገነቡት ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች በተጨማሪ ሌሎች 8 ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ግንባታ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን በማሳተፍ በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት የከተማ አስተዳደሩ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል።