አዲስ አበባ፣ታህሳስ 25፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ተጨማሪ 3 ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳን አስታውቃለች።
ዋሽንግተን ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ስፍራው የላከችውም የኢራኑ ጀኔራል ቃሲም ሱሊማኒ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ በቀጠናው ውጥረት መንገሱን ተከትሎ ነው።
አሜሪካ በትናንትናው ዕለት በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩትን የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒን ኢራቅ ውስጥ መግደሏ ይታወሳል።
የጀኔራሉን ህልፈት ተከትሎም በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ነው የተነገረው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶላንድ ትራምፕ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥የሀገራቸው ወታደሮች ባከናወኑት የተቀናጀ ዘመቻ ቀጠናውን በማተራመስ ግንብር ቀደም የሆኑትን ጀኔራል መግደላቸውን ተናግረዋል።
ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የጦር መኮንኖች እንዲሁም በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲያሴሩ የነበሩ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል ።
ጀኔራሉ የተገደሉትም በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ብሎም በአሜሪካ ዜጎች እና ንብረት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስቆም እንጂ አዲስ ጦርነት ለመጀመር አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ በበኩላቸው፥ የሀገሪቱን ታላቅ ጀኔራል የገደሉ እና እንዲገደል ትዕዛዝ የሰጡ አካላት ከባድ አጸፋዊ ምላሽ ይጠብቃቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ድርጊቱን ተከትሎ ቴህራን ልትወስድ የምትችለውን አጸፋዊ እርምጃ ለመከላከልም አሜሪካ ተጨማሪ 3 ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
እነዚህ ተጨማሪ ወታደሮችም በቅርቡ ወደ ኩዌት የተላኩትን 750 ወታደሮች የሚቀላቀሉ ይሆናል ነው የተባለው።
ምንጭ ፥አልጀዚራ እና ቢቢሲ