አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪፐብሊካን ጥበቃ ሀይል ከእዞች እና ከሌሎች የሠራዊቱ አሀዶች ጋር በመጣመር በህግ ማስከበር ዘመቻው የፈጸመው ግዳጅ ውጤታማ እንደነበር የሀይሉ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ብርሀኑ በቀለ አስታወቁ፡፡
ዋና አዛዡ የሪፐብሊካን ጥበቃ ሀይል በተለይም በራያ እና በምዕራብ ግንባሮች በጁንታው ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ሀያልነቱን አስመስክሯል ነው ያሉት፡፡
አዲቀይህ አካባቢ በነበረው ፈታኝ ግዳጅ የሪፐብሊካን ጥበቃ ሀይሉ የኮማንዶ ዩኒት በጁንታው ጀርባ በኩል ምሽግ ሰብሮ በመግባት የፈጸመው ጀብዱ ለወገን አኩሪ ነበር ያሉ ሲሆን እስከ መቐለ በነበረው ተልዕኮም ውጤታማ ግዳጅ መፈጸሙን አስረድተዋል ፡፡
ሜጀር ጄኔራል ብርሀኑ በምዕራቡ ግንባርም ከሁመራ እስከ ዳንሻ የሚሸሸውን የጁንታ ተዋጊ የማገትና የመቆጣጠር ስራ መሰራቱን በመግለፅ በአሁኑ ወቅትም የተንጠባጠበውን የህወሓት ታጣቂ በማደን ላይ ይገኛል ብለዋል ፡፡
የሪፐብሊካን ጥበቃ ሀይሉ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በተጓዳኝ በምዕራብ ወለጋ እና በመተከል ሽፍቶችን የመደምሰስ ተልዕኮውን በተሳካ መንገድ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
የተካሄደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ፍትሀዊ ስለነበረ እግረኛው፣ ሜካናይዝዱ፣ ልዩ ሀይሉ፣ አየር ሀይሉ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት በጥምረትና በቁርጠኝነት እንዲሁም በብልሀት የጦር አመራር የተፈጸመ ዘመቻ በመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ያኮራ ተግባር ተፈጽሟል ብለዋል ሜጀር ጄኔራል ብርሀኑ።
ህዝቡ እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ ለውጤቱ መሰረታዊ ድርሻ እንደነበረውም ገልጸዋል ፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!