የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርና ሚኒስቴር አርሶ አደሩ የሰበሰበውን የመኸር ምርት ከብክነት ጠብቆ እንዲያከማች አሳሰበ

By Tibebu Kebede

January 03, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሶ አደሩ ከማሳ ላይ የሰበሰበውን የመኸር ምርት ከብክነት ጠብቆ እንዲያከማች የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በ2011/ 12 የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ወደ 90 በመቶ የሚጠጋው መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል ከሚፈጠርባቸው ሁኔታዎች አንዱ በጎተራ ከገባ በኋላ የጥንቃቄ መጓደል በመሆኑ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዳይለየውም አሳስበዋል።

ዘንድሮ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የሜካናይዜሽን አጠቃቀም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው፥ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ ከፍተኛ የህብረተሰብ ተሳትፍ የታየበት መሆኑንም አውስተዋል።

የመኸር ሰብሉ ከማሳ ባልተነሳባቸው ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የሚያሰጋ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደማይኖርም ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በቀጣይ በሰብል ስብሰባው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ሰብሉ በስፋት ከማሳ በተነሳባቸው አካባቢዎችም የመስኖ ልማት ስራው መጀመሩንም ነው የተናገሩት።

መንግስት በመስኖ ሊያለማው ካቀደው 32 ሺህ ሄክታር የስንዴ መሬት ውስጥም እስካሁን 7 ሺህ 500 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗልም ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ በመስኖ ያለማዋል ተብሎ ከታቀደው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥም 600 ሺህ የሚሆነው መልማት መጀመሩንም አስረድተዋል።

በትእግስት ስለሽ