አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በጎርፍ ለተጎዱ ሶማሊያዊያን የመድሃኒት እርዳታ አድርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ ሂር ሸባሌ ክልል በበለደወይን አካባቢ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሶማሊያዊያን ነው አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ የሚሰጡ ሃኪሞችን እና 10 ቶን የመድሃኒት ድጋፍ ያደረገችው።
እርዳታውን በሶማሊያ የኢፌዲሪ ልዩ አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጦፋ ለበለደወይን ዞን አስተዳደር አስረክበዋል፡፡
በርክቡ ስነስርዓት ላይ የሸባሌ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የክልሉ ፓርላማ ምክትል አፈጉባኤ እና በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጦፋ በዚህ ወቅት በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ህዝብ ጎን በመቆም ቀጣይ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለቸ ብለዋል።
የሂር ሸባሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙሀመድ አብዲ ዋሬ በኢትዮጵያ በኩል ስለተደረገው አስቸኳይ የነፍስ አድን ድጋፍ እና በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት የክልሉን ጸጥታና ደህንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ በጎርፍ የተገዱ ሶማሊያዊያንን ለመታደግ ላደረገው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡