የሀገር ውስጥ ዜና

ባለስልጣኑ ለበዓሉ በመዲናዋ የተሻለ የውሃ ስርጭት እንዲኖር ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

By Tibebu Kebede

January 03, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ የተሻለ የውሃ ስርጭት እንዲኖር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር የውሃ መገኛዎች ከዚህ ቀደም በሚያመርቱት የውሃ መጠን ላይ ተጨማሪ 12 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ በማምረት ዝግጅት ማድረጉን ነው ያስታወቀው።

እንዲሁም በካራ፣ ሠላም፣ ቁስቋም፣ ሸጎሌ እና ኪዳነ ምህረት አካባቢ የሚገኙ 5 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በተሽከርካሪ እንዲሞሉ በማድረግ እና ከከፍተኛ ውሃ ተጠቃሚ ተቋማት ውሃ በመቀነስ የተራዘመ ፈረቃ ባለባቸው አካባቢዎች ተጨማሪ የውሃ ስርጭት እንዲኖር ይደረጋል ብሏል።

ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ በማዕከል እና በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የውሃ ምርት እና ስርጭቱን የሚከታተሉ ኮሚቴዎች በማቋቋም እስከ ምሽቱ 5 ሠዓት እንዲሰሩ ይደረጋልም ነው ያለው።

በተመሳሳይ በኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ምክንያት የውሃ ስርጭት ችግር እንዳይፈጠር የመጠባበቂያ ጀኔሬተሮችን ዝግጁ ማድረጉን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።