አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የተጠናው አዲስ ጥናት ይፋ ሆነ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለውጥ ምክር ቤት ውይይት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በሂልተን ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በዚህ ወቅትም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የተጠናው አዲስ ጥናት ይፋ ሆኗል።
በጥናቱ መሰረት 8 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር፣ 15 የትምህርት ተቋማት የአፕላይድ፣ 21 የትምህርት ተቋማት አጠቃላይ እና 3 የትምህርት ተቋማት ደግሞ ስፔሻላይዝድ በሚል ተለይተዋል።
በዚህም መሰረት አዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ሀሮማያ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ እና መቀሌ የጥናትና ምርምር፥ አርሲ፣ አሶሳ፣ አክሱም፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ኮተቤ፣ ጅግጅጋ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሰመራ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ወልቂጤ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አፕላይድ ተብለው ተመድበዋል።
ጋምቤላ፣ መቱ፣ ሚዛን፣ ዋቻሞ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲካተቱ፥ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ስፔሻላይዝ ተብለው መለየታቸው ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት አዕምሯቸውን ሊያበለጽግ የሚችል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ሆኖም ችግሮች የተፈጠሩ ሲሆን ይህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተፈጥረው ለተማሪዎች ህይዎት መጥፋት እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስተጓጎሉንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከፓርላማ፣ ከዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ችግር ወደ ተከሰተባቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መላኩን አስታውቀዋል። ቡድኑም በተቋማቱ የተከሰቱ ችግሮች ታቅደው፣ በጀት ተበጅቶላቸው፣ ስልጠና እና ስምሪት ተሰጥቶ የተከናወነ መሆኑን በምልከታው ማረጋገጡን አንስተዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የዩኒቨርሲቲ ሴኔትም ችግር ፈጣሪ አመራሮችና ሰራተኞች ካሉ እርምጃ እንዲወስድም አሳስበዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ ከሚገኙት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑ በሰላማዊ መንገድ የመማር ማስተማር ስራቸውን መቀጠላቸውን በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ለሁለት ቀናት በሚቆው የተቋማዊ ለውጥ ምክር ቤት ውይይት ላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል።
በዙፋን ካሳሁን