የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ 16 የመንገድ ፕሮጀክቶች እና ድልድዮች ተመረቁ

By Tibebu Kebede

January 03, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ተገንብተው የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እና ድልድዮችን አስመረቀ።

ባለስልጣኑ ያስመረቃቸው ፕሮጀክቶች 16 ሲሆኑ፥ የነባር መንገዶችን ደረጃ ማሻሻልና ጨምሮ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታን ያካተተ ነው።

መንገዶቹ 25 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖራቸው ከ10 እስከ 30 ሜትር ስፋት አላቸው።

ለመንገዶቹና ድልድዮች ግንባታ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፥ ወጪውም በከተማ አስተዳደሩ ተሸፍኗል።

የመንገዶቹ መገንባት የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ በመቅረፍ የከተማውን የመንገድ ሽፋን ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፕሮጀክቱ በከተማዋ የተጀመሩ የመንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንደሚጠናቀቁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ከዋና ዋና መንገዶች ግንባታ በተጨማሪ የመጋቢ መንገዶች ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

በለይኩን አለም