የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ቀድሞ ምርት በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች የመስኖ ልማት መጀመሩ ተገለጸ

By Tibebu Kebede

January 02, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ ቀድሞ ምርት በተሰበሰበባቸው እና ቆላማ  በሆኑ አካባቢዎች  የመስኖ ልማት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮነን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር  ባደረጉት ቆይታ፥በክልሉ  ከ219 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ 30 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ለባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፥ ዘር እና መሰል ግብዓቶችንም ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የልማት ስራው የመስኖ ፕሮጀክቶችን  በመጠቀም፣ ሰፋፊ ኩሬዎችን እና ወንዞችን በመጥለፍ እና አርሶ አደሩ ውሃ ባለባቸው ቦታዎች ጉድጓዶችን እንዲቆፍር በማድርግ  የሚከናወን መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም  የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ክልሉ ከፌዴራል እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው

አሁን ላይም ፕሮጀክቶቹ የሚገነቡባቸው  ዞኖች  የተመረጡ ሲሆን ፥በተያዘለት  ጊዜ እንዲጠናቀቅ  የሚያስችል ጥናት በማቅረብ  እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን በጀት በመመደብ  የመስኖ ልማት ንቅናቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ  ተጠቁሟል።

በዙፋን ካሳሁን