Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህግ የበላይነትን፣ የገጽታ ግንባታ እንዲሁም አጋርነትና ትብብር ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 8፣ 2013( ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሠላምና ደህንነት፣ የህግ የበላይነትን፣ የገጽታ ግንባታ እንዲሁም አጋርነትና ትብብር ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገለፀ፡፡

ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የሶስት ወራት እቅድ ላይ ከፌደራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ከተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መክሯል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዓመት የማይሞከሩ ስራዎችን በጥናትና ምርምር በመታገዝ በከፍተኛ ርብርብና ቅንጅት በአጭር ጊዜ ማከናወን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ሶስት ወራት ተቋሙ ሠላምና ደህንነትን እንዲሁም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፤ የሠራዊቱንና የተቋሙን አቅም መገንባት፣ የተቋሙ ቀጣይ እይታና የገጽታ ግንባታ እንዲሁም አጋርነትና ትብብር በሚሉት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚያከናውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች የእቅዱ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የፖሊስ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲን በቀጣይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎችን በመረጃ እንዲመራ በአዲስ መልክ የፖሊስ መረጃ አደረጃጀትና አሰራርን በመዘርጋትና በመተግበር እንደሚሰራና ቀጣይ ምርጫ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በስኬት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉም ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ፌደራል ፖሊስ በኦሮሚያ ክልል ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር በተያያዘ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል፣ በደቡብ ጉራፈርዳና በሌሎችም አካባቢዎች ባለው ስምሪት ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በአጭር ጊዜ ስኬት ለማስመዝገብ እንዲቻል በፅናትና ቁርጠኝነት እንዲሁም በተጠያቂነትና በሀላፊነት ስሜት መሰራት አለበትም ነው ያሉት፡፡

አዲስ አበባ ከምንም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ትሆን ዘንድ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም የራሱ ማንዋልና ቢሮ ያለው የሥራ ክፍፍል ተቋቁሞ ወደ ስራ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም የወንጀል አሰራር ሂደቶች እየረቀቁ የመጡና በቴክኖሎጂ የሚደገፉና ወደ በይነ መረብ ደረጃ እየደረሱ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ ልክ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆን ምርመራውን ማከናወን የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ተገቢ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) ፣ ከተባበሩት መንግስታት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥብቅ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም የውጭ ሀገራት የፖሊስ ስምሪት ለመጀመር አስፈላጊው ጥናት ተካሂዶ ዝግጅቱ መጠናቀቅ እንዳለበት አውስተዋል፡፡

በቀጣይም የምድር ባቡር፣ የአቪዬሽን፣ የዩኒቨርሲቲ፣ የድንበር ደህንነት፣ የጎብኚዎች እና የኢንዱስትሪ ፖሊስ የስራ ክፍሎች እንደሚከፈቱ መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version