አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሁለት ትምህርት ቤቶች ባደረገው የመስክ ምልከታ በመማር ማስተማር ስራው ኮቪድን አስቀድሞ ለመከላከል ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የድሬዳዋን አጠቃላይ 2ኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት እና የምስራቅ ጀግኖች መታሰቢያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተዘዋውሮ በጎበኘበት ወቅት ኮቪድን ለመከላከል የተማሪዎችን የመማሪያ ክፍሎች፣ አደረጃጀት እና የአፍና የአፍንጫ አጠቃቀም፣ በመውጫና መግቢያ በሮች ላይ የውሃ አቅርቦት እና የኮቪድ ሙቀት መለኪያ ማሽን መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡
ኮቪድን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ በሁለቱም ትምህርት ቤቶች ለወላጆች እና ለተማሪዎች እንዲሁም ለመምህራን እና ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አረጋግጠው ቋሚ ኮሚቴው የድሬዳዋ አጠቃላይ 2ኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ኮቪድን ለመከላከል የለይቶ ማቆያ ክፍል ማዘጋጀቱንና በአንጻሩ የመማሪያ ክፍሎች መጣበብ መኖሩን ታዝቧል፡፡
የድሬዳዋ አጠቃላይ 2ኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፍቃዱ ሰንበታ እንደገለጹት የ12ኛ ክፍል ሃገር ዓቀፍ ፈተናን በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ለመስጠት በሚደረገው እንቅስቃሴ መፈተኛ ክፍሎች ቢዘጋጁም የሰርቨር እና የታብሌት አንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች እንዳልተሟሉ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው ኮቪድን በመከላከል የመማር ማስተማር ስራውን በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፤ በ38 የገጠር ቀበሌዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ ግንዛቤ መሰጠቱን እና ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡
ከስደት ተማላሽ ለሆኑ ዜጎች የለይቶ ማቆያ በነበሩ ስምንት ትምህርት ቤቶች የደረሰባቸውን የወንበርና የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶች ውድመት የመጠገን ስራ መከናወኑን ያስረዱት ወይዘሮ ሙሉካ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ 850 ተማሪዎች ምገባ በምግባረ-ሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል አገር ዓቀፍ ፈተናውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመስጠት የታሰበ ቢሆንም፣ እስካሁን የሰርቨር፣ የታብሌት እና መሰል ግብዓቶች በተለያየ ምክንያት ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው ለትምህርት ቤቶች ተደራሽ እንዳልሆኑም መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!