የሀገር ውስጥ ዜና

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር  ፍቅረስላሴ ወግደረስ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

By Tibebu Kebede

December 16, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፍቅረስላሴ ወግደረስ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ።

የቀብር ስነ ስርዓታቸው በመንበረ ፀባኦት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረስላሴ ታህሳስ 3 ቀን 2013 በ75 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ አየር ኃይልን በመወከል ደርግን ከመሠረቱት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው።

ሻምበል ፍቅረስላሴ ከረጅም የእስር ህይወት በኃላ “እኔና አብዮቱ” እና “እኛና አብዮቱ” የተባሉ ሁለት መፅሀፍትን ለአንባቢያን አቅርበዋል ።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ወጣት ካዴት ሆነው በመግባት በ1955 ዓ.ም የተመረቁ ሲሆን በአሜሪካ ሀገርም ስልጠና ወስደዋል።

በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ሀገራቸውን ያገለገሉት ፍቅረስላሴ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አደራጅ ኮሚቴና የደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና ከጳጉሜን 5 ቀን 1979 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 29 ቀን 1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!