Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

በወቅቱም አቶ ደመቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም በመውሰዳቸው ኢትዮጵያ ያላትን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ እና አሁናዊ ሁኔታ አብራርተዋል።

በዚህም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት፣ የቢሮክራሲያዊ መዋቅርን እንደገና በማደራጀት እና በክልሉ ለሚኖሩ ህዝቦች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት መጀመሩን ገልጸዋል ፡፡

በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ክልሉ ያደረጉት ጉብኝት እና ከጊዜያዊ አስተዳደር ጋር መወያየታቸው ክልሉ ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሰ መምጣቱን አመላካች ነው ብለዋል።

አያይዘውም በክልሉ የተካሄደው የህግ ማስከበር ዋና ስራ መጠናቀቁን እና አሁን ላይ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል የፖሊስ ስራ ብቻ መቅረቱን አስረድተዋል።

አሁን የመንግሥት ዋና ትኩረት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋም እና መልሶ መገንባት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግስት በአንዳንድ አካባቢዎች የስልክ እና የኤሌክትሪክ መስመሮችን መመለሱን ጠቁመው÷ የወደሙ መንገዶችን እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን መልሶ ለማቋቋም ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

አቶ ደመቀ በክልሉ ያሉትን ሰብአዊ ጉዳዮች በተመለከተም በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ፣ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ሥጋቶች ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ በኤርትራ ስደተኞች ላይ የተነሱትን ስጋቶች በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት መንግስት በቅርበት እያጠና መሆኑንም አረጋግጠዋል ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ÷ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም መልህቅ ነች ብለው እንደሚያምኑ እና የኢትዮጵያ መረጋጋት የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

ባለስልጣናቱ አያይዘውም አቶ ደመቀ ውይይቱን በማመቻቸታቸው ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version