አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመከላከያ የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በጦር ኃይሎች ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን ጎብኝቷል።
መከላከያ ሠራዊቱ ህግ ለማስከበርና ለህልውና ባካሄደው ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸው አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛል፡፡
በጦር ኃይሎች ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምና ላይ ያሉትን አባላት ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሚኒስትር ዲኤታዎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት በሥፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋቸዋል።
ለመከላከያ የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል “ለኢትዮጵያ ክብር በዱር በገደሉ የተዋደቃችሁ የቁርጥ ቀን ልጆች ስማችሁ ሁልጊዜም በታሪክ መዝገብ ተከትቦ ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይ የነበሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለሠራዊቱ ያላቸውን ክብር በከፍተኛ ስሜት የገለፁ ሲሆን የሠራዊቱ አባላትም ሕዝቡ እያሳየ ላለው ወገናዊነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ኮሚቴው የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ ሲሆን በቅርቡም ድጋፍ ለሚሹ የሠራዊት አባላት ድጋፍ የመስጠት መርሃ ግብር እንደሚጀምር ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።